ታዋቂ ልጥፎች

ገፆች

2014 ኦገስት 1, ዓርብ

“ሰው ለሰው” ድራማን ሰው ለሰው ያስባለው ምን ይመስላችኋል፤



እንደምን አላችሁ፡፡ እነሆ! ተፈጸመም አይደል፡፡ እኛ ለዘመናት መጨረሻውን ማወቅ ስንናፍቅ መጨረሻውን በሁለት ጣታቸው ይዘው እያሾሩ “እንቁልልጮ!” ሲሉን ... እንደ ጸደይ ጎሕ ቀን በአሳባችን ሌት በሕልማችን እስኪመጣብን ድረስ የናፈቀንን መጨረሻውን አሁን አየንም አይደል፤… ታዲያ አቶ አስናቀ አሸብርም ተንጠለጠሉ አይደል፤የተፋቀረውም ተፋቅሮ
የተዋለደውም ተዋልዶ፣ሸቤ የሚወርደውም ወረደ አይደል፤ … እስኪ ታዲያ እኛም በተራችን “ይህ ከኾነ ዘንዳ ሰው ለሰው ድራማን ሰው ለሰው ያስባለው ምንኛው ነው”  ብለን እንጠይቅ፡፡ በዚያውም እንደነሱው “እንቁልልጮ” ኹሉ የእኛም እንደ “ድንቄም … !” ትቈጠርልናለች፡፡ 

ታዲያ ይህን ጥያቄ ስትጠይቁ አደራችሁን ደራሲዎቹን እርሷቸው፤እነርሱ “ሰው ለሰው” ያሉበት የራሳቸው ብዙ ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በዚያ ላይ ሲያቀብጠን ጠይቀናቸው ደግሞ ርእሱን ለማብራራት ”ከታሪካዊ አመጣጡ” ጋር ባለ መቶ ሠላሳ ምናምን ክፍል ማብራሪያ እንዳይፈረድብን፡፡ ከቻላችሁ እንደውም አረሳሷቸው፡፡ 

ልጀምር ነው … ጀመርኩ! 

ርእሱን ልብ ብላችሁ ስታዩት በጅምር የቀረ እንደኾነ ታያላችሁ፤ሰው ለሰው … ፡፡ እኔ በበኩሌ ሁለት አቅጣጫዎች ይታዩኛል፡፡ “ሰው ለሰው … መድኃኒቱ ነው”  የሚለው አንደኛው ነው፡፡ ሌላኛው ያው “ሰው ለሰው … ጠንቁ ነው”፡፡ ርእሱን መጨረስ ታዲያ እንደየስሜታችን ነው፡፡ ምንም ብትሉ ግን ከሁለቱ ውልፍች አትሉም፡፡ በዚህም ወረደ በዚያ “ሰው ለሰው” ድራማ የሰው ልጆች አንዳችን ለአንዳችን ምን እንደኾንን ሊነግረን ፈልጎ ትቶታል፡፡ ይሄ በጅምር የቀረ ዓረፍተ ነገር ወይም አሳብ የሚባለው ነው፡፡ እንደውም የ4ኛ ክፍል አማርኛ ትምህርት ላይ እንደተማርነው፤ ... ማነው እስኪ አምጡት … እ!  “ሐረግ”፡፡ ምስጋና ይግባቸውና አማርኛ መምህሬ አቶ ተሻለ ይህቺን ውብ አድርገው ነው ያስተማሩኝ፡፡ እንዲያውም የፊታቸው ለዛ እና ፍንጭት ብጤአቸው አሁንም ትዝ ትለኛለች፡፡ 

በአንድ በኩል እነ አቶ አስናቀን ካየን አፋችንን ሞልተን ሰው ለሰው ጠንቁ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ምን እርሳቸው ብቻ እነ አቶ መስፍንንም ብናይ እንደዚያው ነው፡፡ ታዲያ! እሳቸውም አይደሉ ለአቶ አስናቀ ጠንቅ የኾኑባቸው፤ ከጠንቅም ጠንቅ ነውንጂ  …. ውይ! ውይ! ውይ! … ትዝ አለኝ እናንተ አቶ አስናቀ አሸብር ለግንባታ ሥራ የተወጠረ መቃ ላይ እንደሮያል ፍራሽ ሲንጋለሉበት፡፡ ከኮሚሽነሯ ጋር የቡሩኬ ውድ መዲ ሮጣ ደርሳ ቢኾን ኖሮ “እንቅልፌ የሰላም የሚኾነው … “ ብላ ታዜምላቸው ነበር፡፡ 

ወደነገሬ ልመለስና “ሰው ለሰው” ድራማ ላይ ታዲያ “ጠንቅነት” ከ ”መድኃኒትነት” ይልቅ በተሳካ ኹናቴ ተሥሏል፡፡ መጥፎዎቹም በጥሩዎቹ ላይ በተሳካ ኹናቴ ጠንቅ ኾነውባቸዋል፡፡ ጥሩዎቹ ሰዎችም የአቅማቸውን ያክል በመጥፎዎቹ ላይ እንደዚሁ፡፡ ሰው ለሰው … መድኃኒቱ ነው የሚለውን ካየን ግን በመርሕ ደረጃ ብቻ ይመስላል - ያኔ እንደውም ከነዚያ ስዶች ጋር የድንበር ውዝግቡን ለመፍታት ስንተባበርና ምክረሐሳቡን ስንቀበል በመርሕ ደረጃ ምናምን … ትዝ አይላችሁም፡፡ አዎን! … “መድኃኒትነት” ድራማው ላይ ሰጥቶ በመቀበል ላይ ተመሥርቶ ብቻ በመርሕ ደረጃ ነው የተተገበረው፡፡ እስኪ ለምሳሌ እናንተ ከገጸ ባሕርዮቹ ኹሉ የረባ መድኃኒት አይታችኋል? አላያችሁም:: … የረባ ጠንቅ ግን በገፍ ነው ያየነው፡፡ በእርግጠኝነት አቶ አስናቀ ብቻቸውን እንኳ 16 ወፋፍራም ጠንቅ ይወጣቸዋል፤እኔ በበኩሌ የዚያ ሠሙን ወተት ምናምን ትቼ ነበር፡፡ እውነቴን ነው! ከላሟ ጡት ላይ በቀጥታ ጥባ ቢሉኝ እንኳ የአገልግሎት ዘመኑ ምናምን … እኔንጃ! አይመስለኝም!፡፡ ሌላ ሌላውን ትታችሁት “ወተቱ ግን ይህን ያክል ሊረክስ እንዴት ቻለ፤” አይደል የተባለው፤እናንተስ “እንዴት በነጻ የላሟን ጡት ጥባ ልትሉኝ ቻላችሁ”… ያን ሠሙን ያለበቂ ምክንያት ጥሩ የሚኾንልኝን ኹሉ ግንባሬን ዘመም፣አፍንጫዬን ቆልመም፣ዐይኖቼን ሰለል፣ከንፈሬን ጥርሴ መሃል ሸጎጥ አድርጌ … [ያው! ልክ እንደኢንስፔክተር ማለት ነው …] በጎሪጥ ማየት አመል መጥቶብኝ ነበር፡፡ መንገድ ላይ ስሄድ እስክሪብቶ የጣልኩ እንደኾን “ወንድም ጣልክ!” ሲሉኝ ዘወር እልና “እንዴት እንደዛ ልትለኝ ቻልክ!” … ሰው ለሰው ጠንቁ ነው የሚለው ድራማው ላይ ጎልቶብኛል፡፡ 

ስለዚህ እኔን እንደታየኝ ከኾነ “ሰው ለሰው” የሚለው ርእስ ምድቡ እንደተማርነው በጅምር የቀረ ዓረፍተ ነገር (ሐረግ) ነው፡፡ ታዲያ ሐረግ አሳቡን ያልቋጨ ዓረፍተ ነገር ነው ብለናል፤ለምሳሌ “አበበ በሶ … ብሎ ያቆመ፡፡ እናንተው ወይ “… በላ” ወይ ደግሞ “… ለበሰ” ብላችሁ ትጨርሱታላችሁ፡፡ ሙሉ ዓረፍተ ነገር ቢኾን ኖሮ የኾነ ዓይነት ዕረፍት ወይም መቋጫ ይኖረው ነበር ... ዐራት ነጥብ፡፡ ይህ ግን የለውም፡፡
ለነገሩ “ሰው ለሰው” እንኳን ርእሱን ታሪኩንም አልጨረሰልንም፡፡ ስለዚህ ርእሱ እንደ አቶ ተሻለ የአማርኛ ትምህርቴ “ሐረግ” ሲኾን ታሪኩም ቢኾን ደግሞ የኾነ የተክል ዓይነት ነበር … ይሄ ግድግዳ እየታከከ ማለቂያ በሌለው አኳኋን የሚያድገው ጅል የደጅ አትክልት … ማነው! ጥሩልኝ … ይሄ በረንዳችን ላይ ተክለነው ጎረቤት ርስት ላይ ጭምር እየተንሰራፋ የሚያወዳጀን … እ! .. እርሱም “ሐረግ” ነው፡፡ እንዴት እንደኾነ ቀላል ነው፡፡ ሐረግ አስተዳደጉ መረን ነው፡፡ ሥርዓት፣ድንበር፣ወሰን፣ምናምን ብሎ ነገር የለውም፡፡ የሞቀውን ጥግ ተከትሎ መትመም ልማዱ ነው፡፡ እናንተ ራሳችሁ እዚያም እዚህም ምስማር እየመታችሁ መንገድ ታበጃጁለታላችሁ እንጂ እርሱ ማደጉን አያቆምም፡፡ ታዲያ .. ሰው ለሰውን ምን ለየው፡፡ እነሞገሴም አይደሉ እዚያም እዚህም “ኳ! ስክት!” እያደረጉ ለዚህ ያበቁት፡፡ አይዟችሁ ሺህ ዓመት አላወራም፡፡ 

ሌላው “ሰው ለሰው” ሐረግነቱ የሰው ልጅ የዘር ሐረግንም ይመስላል፡፡ የኹላችንም የዘር ሐረግ ቊጠሩት ብንባል ወደላይ ማለቂያው በሚያደክም አኳኋን እስከ አባታችን አዳም ድረስ ይቈጠራል፡፡ ወደታችም ቢኾን መካን እስካልኾን ድረስ ዝም ብሎ ይቈጠራል፡፡ እኛ ብንተወው ልጅ የልጅ ልጆቻችን ይቈጥሩልናል፡፡ ይሄኔ ነው ታዲያ “ምስጋና ለእነርሱ … ያቺን 'ቀጭን ትእዛዝ' ቶሎ ላስተላለፉልን” ማለት፡፡ አለዚያማ “ሰው ለሰው”ስ ቢኾን ለዘራችን ሊተርፍ አልነበር፤መቼ እንደዛ እንደመሸባት ጎሕ ድንገት ከዐይናችን ይሰወር ነበር፡፡ እኔ በበኩሌ ወንዳታ ብያቸዋለሁ፡፡

“ሰው ለሰው” ርእሱን በጅምር መተዉ አጠቃላይ የድራማውን አረዳድ ተመልካቹ በመሰለው እንዲተረጒመው ሰፋ ያለ እድል ሊሰጥ ይመስልና .. ሳይመስል ይተወዋል፡፡ … ምክንያቱም ለተመልካች አረዳድ እድል ለመስጠት ከኾነ ታሪኩ አቶ አስረስን ሳያክል እንደነ ጎራው መለስ ያለ ይደረግ ነበር፡፡ ያኔ ነው እኛ እድል አግኝተን በመሰለን የምንሸከሽከው፤የምናረዛዝመው፡፡ ለተመልካች እድል ሰጥቶ ሁለት ሦስት ዓመት በታሪክ ግጭት ማድበን ... ለማጉረስ ሰንዝረው እንደሚጎርሱት ዓይነት ጨዋታ ማለት ነው፡፡ እየጐረሱም እያየናቸው ወዝ በወዝ የኾኑት ብዙ ናቸው፡፡ 

ምን አለፋችሁ “ሰው ለሰው” ወዶ ይኹን ተሸውዶ እንጃ እንዲሁ ማብቂያቸው ሕልም ሕልም የሚሉና ረጃጅም ነገሮችን መርጧል፡፡

እግረ መንገዴን ግን የአገሬን የጥበብ ሰዎች ትንሽም ሳላደንቃቸው አላልፍም፡፡ እንኪያስ ታዲያ! የምር ካልኾነ በስተቀር ፊልሞቻችን ላይ በጨፈቃ የተቦተረፈ ሆድ አይተን እናቃለን እንዴ፤ወግ ደረሰንኮ እናንተ፡፡ ልብ ብላችሁ ሌሎቹን ፊልሞች ካያችሁ የመረረው አክተር ካለ ጩቤ ይይዝና ፊቱን ጨምደድ አርጎ ወደላ….ይ አንሥቶ ሆሊዉድ ላይ እንደለመደብን “ሆዱ ላይ ሰመጠጠው”  ስንል እጉያው ሻጥ አድርጓት የሚንጋለል፡፡ ታዲያ የየትኛውም ኢትዮጵያዊ አክተር ሆድ ከሴንጢም ኾነ ከመቃ ጋር የእኛን የፊልም አድናቂዎችን ዐይን ደፍሮ ተጋፍጦን አያውቅም፡፡ እንዲሁ ብቻ ምሬትና ቁርጠኝነቱን ፊቱ ላይ ያስነብበንና ወይ መብራት ይጠፋብናል ወይ ጀርባውን አሽሮን በፊቱ ይደፋል፡፡ … ፎጋሪ ኹላ! 

እባካችሁ የኢትዮጵያ የጥበብ ሰዎች! ለወደፊቱ እንደዚህ ቶሎ የማያልቅ ነገር አትሥሩ፡፡ ቶሎ የማያልቅ ከኾነባችሁ እንኳን ዘግይቶም ቢኾን ግራ የማያጋባ አስተላለቅ መምረጥ ብልህነት ነው፡፡ ሲጎተቱ ኖረው አስራ አንድ ሰዓት ከዐርባ ዘጠኝ ደቂቃ ላይ ድንገት መሐመድ አማን መኾኑ አዋጭ አይደለም፡፡ ውድ አንባቢዎች! እኔም ቶሎ ላቁም፤የድራማው አንሶ … … ለማንኛውም በአጭር የስልክ መልእክታችሁ ተዋናዮቹን መምረጣችሁ ላይ ጠንክሩ፡፡ እኔ የስልክ አድራሻዎቹ ጠፍተውብኝ ትቸዋለሁ፡፡ ያው እነሱም ሐረጎች ናቸው፤ዘለግ ዘለግ ያሉ … ኤስ.. .ደብልዩ… ዶት…. ምናምን፡፡ ቸር ቆዩ!

Comment on this