ታዋቂ ልጥፎች

ገፆች

2014 ኦገስት 19, ማክሰኞ

(የልጅነት ወግ) ቡሄ ሲመጣ እኔን ትዝ የሚለኝ



አይ ልጅነት! አይ ሆያ ሆዬ! አይ ያሚ ሜዳ … አይ ሞደርን ሰፈር፡፡ አይ ጥይት ቤት .. አይ አይ አይ … ሙልሙል በችርቻሮ የሸጥንበት ጊዜ … 
 
የምንጨፍርበት ዱላችን ከምት ብዛት ሥሩ ሥር ያበቀለ እስኪመስል ጭራሮ ኾኖ፡፡ ዱላ እጁ ላይ ያለቀበት ጨፋሪ እኮ ነበረ መሃላችን፤ … የገነት አቡሽ፡፡ ጠዋት መጨፈር የጀመርን ሰዓት በጨመረ ቁጥር ዱላው እያጠረ፣ እሱም እያጎነበሰ … ማታ ላይ አቡሽ ለምንጨፍርበት ቤት ቤተኞች የአክብሮት ሰላምታ እየሰጠ እንጂ እየጨፈረ በፍጹም አይመስላቸውም ነበር፡፡ እሱም ግን መሬቱን በጣም
ይመታው እንደነበረ ትዝ ይለኛል፡፡ አንደኛው ቤት ጨፍረን ወደሌላ መንገድ እየሄድን እንኳ መሬት እየደቃ ማንም ሳያወጣ “ሆ!” እያለ ይሄድ ነበር፡፡ እነ አብነት ቤት እንደውም ገና እንደደረስን ሆያ ሆዬ ሳይባል “ሆ!” ብሎ የደጃቸውን የጣውላ ንጣፍ ያለአግባብ ሲደቃው ኤርሚያስ የተባለው የቤቱ ጎረምሳ ከጓዳ ወጥቶ በኩርኩም ብሎ እንዳባረረውና “እናንተ ቀጥሉ!” ብሎን ሲዞር … እኛም ቆሌአችን ተገፍፎ መጨፈር አይበሉት ተንጫጭተን እንደተመለስን ትዝ ይለኛል፡፡ የኾነች ሙልሙል ተሰጠችንና ኩርቱ ፌስታላችን ውስጥ ቀላቀልናት፡፡

ሙልሙል ባየሁ ቁጥር መቼም ቢሆን እሷን ሙልሙልና ሞገስን አልረሳውም፡፡ ከሰፈሩ ጉልቤዎች አንዱ ነው ሞገስ፡፡ ከጀለሶቼ ጋር በኩርቱ ፌስታል ካጠራቀምናቸው ባለብዙ ቀለም የበቆሎ፣ የስንዴ፣ የገብስ፣ የዘንጋዳ፣ ጥቁር፣ ነጭ፣ ቀይ፣ ዳለቻ፣ … ሙልሙሎች መካከል ያሃቺ ተአምረኛ ሙልሙል ነበረችበት፡፡ ሞጌ አስቆመንና “እስቲ ክፈተው!” አለን፡፡ ፌስታሉን የያዘው በሌ ነበር፡፡ ደንፉው ፊቱ ላይ በደምብ እየተነበበ ፌስታሉን ከፍቶ አሳየው፡፡ በሌ ደንፉ ሲይዘው ዐይኑ ስለሚቀላ በጣም ያስፈራል፤ልጅ ቢኾንም፡፡ የእኛ ዐይን ቁልጭ ቁልጭ ቢል እንጂ እንደዛ አይቀላምም፣አያስፈራምም … የኹላችንም እንደበሌ ቢቀላማ ኖሮ ሞጌ አይደለም ሲ.አይ.ኤ. ባልደፈረን ነበር፡፡ ታዲያ እጆቹን ልኮ ዳበስ ዳበስ ሲያደርግ ዐይኑም እጁም ያረፈባት እንደ እንቁላል ነጭ ኾና ለመብላት የምታሳሳውን ከነ ጋሽ ፈጠነ ቤት የተሸለምናትን ሙልሙል ነበር፡፡ 

እያገላበጠ አያትና ጥርሱን እየሳለ ምራቁን ሲውጥ ሊፈርድባት እንደኾነ ገባን፡፡ እኔ በበኩሌ ተስፋ ቆረጥኩ፡፡ እውነት ለመናገር ያቺን ሙልሙል እነጋሽ ፈጠነ ቤት ስንቀበላት ሙልሙል ሁሉ አልመስል ብላን ተቸግረን ነበር፡፡ ያው እንደተለመደው በልጅ እግራችሁ ሮጥ በሉና አድርሱ ተብለን የተላክን እንጂ በዚያ ወግ በማያውቅ ጣቻችሁ ፈትላችሁ ማዕረግ በሌለው አፋችሁ አኝካችሁ … እራሳችሁ ብሉት የተባልን አልመሰለንም ነበር፡፡ ታዲያ እንደተቀበልናት በመካከላችን “ይበላ!” እና “አይበላ!” በሚል የጸና ሙግት ገብተን እንደውም ከመካከላችን እንደ ኤርትራ የራሳቸውን እድል በራሳቸው ሊወስኑ የፈለጉም እንደነበሩ ትዝ ይለኛል (ደግሞ ዘመኑም ሩቅ ስላልነበረ ፋሽን ነበር እሱ ነገር)፡፡

ታዲያ እኔ ዲፕሎማት ቢጤም አደለሁ! ወደሪፈረንደም ከመሄዳችን በፊት አስቀድሜ ልክ እንደ ባለራእዩ መሪያችን “ማንዴላን ማን አሠለጠነ! … ሙጋቤን ማን ረዳ!” እንደሚሉት በኋለኛው ዘመን እኔም አፌን ሾል አድርጌ “ሆያ ሆዬ ማን አለ! .. እ! … ሆ የኔ ጌታ ማን አለ! … እ!” ብዬ ላነቃቃ ሞከርኩና ከዚያ ቀጥሎ የሚባለው ነገር ጠፍቶብኝ አፌ ሲስለመለም ጀለሶቼ እንደጉድ ባትኩሮት ከጠበቁኝ በኋላ ነጥብ ሲያጡብኝ በንዴት ባለ ብዙ ቀለማቱን የድሃ የሃብታም ጎረቤት ቅልቅል ሙልሙል በየተራ እያነሡ ፊት ፊቴን ሲነርቱኝ … ያው ምግብ ያፋቅራል አደል! በተለይ ፉድ ፋይት! … እኔን በመደብደብ ተፋቅረው በዚያች ምስኪን ሙልሙል ሰበብ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ከመፈራረስ ዳነ፡፡ ሙልሙሎቹም ተለቃቀሙና ተመልሰው ኩርቱ ውስጥ ገቡ፡፡ 

ይሄኔ ነው ታዲያ ሁለት እርምጃ ተራምደን ታዴ ሱቅ ስንደርስ ሞገስ ከጋሼ ሐድጉ የጎማ ዛፍ ሥር ብድግ ብሎ “ና እስቲ!” ብሎ የጠራን፡፡ አይ የንቀቱ ንቀት፡፡ ያሃ ኹሉ ፈልፈላ እንደ አንድ ተራ ጨቦ “ና!” … 

ታዲያ ያሃቺን እንደ ነጭ የእርግብ ጫጩት የሳሳንላትን ሙልሙል ሞጌ ጨብጦ ከንፈሩን ሲያሾልና ጥርሶቹን ሲስል ዘብጥያ ልትወርድ እንደኾነ ባነንን፡፡ ከኹላችንም በሌ ነቃ ያለ ነበር፡፡ በተለይ ገንዘቦች ላይ በምናደርገው እንቅስቃሴ ኹሉ የሱ ብልጠት ባይኖር ኖሮ አሳባችን ኹሉ ቅብጠት በነበረ፡፡ ምን ያደርጋል … ይቺን ሙልሙል ከሞጌ መንጋጋዎች ካላዳነ ታዲያ የሱ ብልጠት ብክነት ነው፡፡ ይሄኔ ነው ታዲያ በሌ ቀልጠፍ ብሎ “እሷ 40 ሣንቲም ብቻ ነች!” ያለው፡፡ ሂሂሂሂሂ … አይ በሌ! ስልቱን አድንቄዋለሁ፤ በነጻ ዘብጥያ ከምትሄድ ቢያንስ የኾነ ዋጋ ይገኝባት ብሎ ነው፤ ታዲያ አይመነትፈው ነገር… ይሄን ሰላቢ! ችግሩ ታዲያ 40 ሣንቲሙ ላይ ነው፡፡ 40ሣንቲም ያኔ የአንድ ቤተሰብ ቁርስ መግዛት ትችላለች፡፡ ታዲያ በሌ ገንዘቡን አበዛው፡፡ እኔም በልቤ “በሌ ደግሞ! ሒሳብ አልተጀመረም እናንተ ክፍል! ፊደል ብቻ ነው እንዴ!” ለነገሩ እኔ ተረድቼዋለሁ፡፡ እናንተ ሙልሙሏን ስላላያችኋት ነው፡፡

ከዚያ በኋላ ሞጌ “40 ሣንቲም …!” እያለ ወደአፉ አስጠጋና ዐያኖቻችን እያዩ በነዚያ እርኩስ ጥርሶቹ ሲገዘግዛት ማመን ተሳነኝ፡፡ ምን እንዳልኩኝ ታውቃላችሁ “ወይኔ እናቴ!”፡፡ ሀቢቦ አፍንጫውን ነፋ … ሲራክ አፉን ከፍቶ ቀረ … የበሌ ዐይኖች እሳት አበቀሉ … እኔ ሕልም ዓለም ውስጥ ገባሁ፡፡ የገነት አቡሽን አየሁትና በሆዴ “ይሄ የያዝከው ዱላህ እስኪያጥር ድረስ መሬት መደብደብ ነው ሥራው! ወንድ ካለህ ይህቺን ምስኪን ሙልሙል አትታደጋትም ነበር” ስንት የተደባደብንላት ሙልሙል ግብዓተ ጨጓራዋ መፈጸም ጀመረ፡፡ ሞጌ አንድ ይገምጥና ቀና እያለ “40 ሣንቲም … !” ይላል፡፡ እያንዳንዱን ጉርሻ 40 ሣንቲም! የሚለው አጥንት ሰንጣቂው ሽሙጥ እየተከተለው የመጨረሻዋ ጉርሻ ላይ ያሃቺ በእውን ዓለም የምናውቃት ሙልሙል በውለታ ቢስ ጎረምሳ እጅ ወደሕልም ዓለም ተሸጋገረች፡፡ 

ሞጌ ምሳውን ፊታችን ከበላ በኋላ አፉን ጠራርጎ እጆቹን እያራገፈ ቀኝ ኋላ ዞሮ ሲያቀጥነው ብቻችንን ኾንን፡፡ ከነበርንበት ኹናቴ አንጻር 1 ብርጌድ ወታደር ትቶን የሄደ እንጂ ሞጌ ብቻውን አልመሰለንም፡፡ ደግነቱ በሌ አሁንም የልብአውቃ ነው፡፡ ማለቴ የልብአውቆ፡፡ ከየት ከየት እንደመጣለትና መቼ እንደተደራደረ ሳናውቅ አርአያ ለሚባል አንድ ምስኪን ጎረምሳ (የጎረምሳም ምስኪን አለው) ሁለት ሙልሙል በሦስት ብር ሸጦ መጣ፡፡ ካፒታላችን በሁለት ዲጂት አደገልን፡፡ ደስ አለን፡፡ ቡሄ ሲመጣ ትዝ የሚለኝ ይህ ነው፡፡ ቸር ቆዩኝ!

Comment on this