ታዋቂ ልጥፎች

ገፆች

2014 ሴፕቴምበር 9, ማክሰኞ

እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ፡ “እኛና የኢትዮጵያውያን የጊዜ ቀመር”



ሮም በጥንታዊው የዓለም ታሪክ ውስጥ ግዙፍና ተጽዕኖ ፈጣሪ አገር እንደነበረች በየትኛውም የታሪክ ትምህርታችሁ ሳይነገራችሁ አላለፈም፡፡ ይህች ታላቅ አገር የሥርዓትና የሕግ ሁሉ መፍለቂያ ነበረች፡፡ እዚያ የተወራው ተራ ወሬ በመላው ዓለም ርዕሰ ዜና ይኾን ነበር፡፡ ሮም ትኩሳት ከተነሣባት መላው ዓለም በረዶ መነከር ይጀምራል፡፡ ሮምን ጉጠት ጋጥ ካደረጋት መላው ዓለም በንፍፊት ያልቃል፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ ሮም የረጨችው ደም ነው ደም ኹኖ የቀረውን ዓለም በሁለት እግሩ አቁሞ እንደሰው የሚያራምደው፡፡ ታዲያ የታሪክ ጠበብት
ናቸው እንጂ እኔ እንደዚህ አላልኩም፡፡   

ዘመን ሲቈጠር ሲቈጠር ኖረና ልክ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ532 ዓ.ም. ላይ ከዚህች ከትኩሳት አገር አንድ መነኩሴ ተነሣና ዐይን የሚያስፈጥጥ አንዳች ክስ አቀረበ፡፡ ክሱ ጠንከር ያለና ባለፈው ትውልድ ላይ ኹሉ የተሰነዘረ ነበር፡፡ መነኩሴው ዲዮኒሰስ ኤግዚጉኒስ ይባላል፡፡ ይህን ክሱን ይዞ የሮም ሊቀ ጳጳስ ዘንድ ቀረበና አንድ አለ፡፡ “እስከዛሬ ድረስ ተሸውደን ነበር፡፡ ክርስቶስ የተወለደው በእርግጥ ተወልዷል ብለን ከምናስብበት ዓመት ቢያንስ 7 ቢበዛ ደግሞ 8 ዓመት ቀደም ይላል” አለ፡፡ “ታዲያስ!” አሉት ጳጳሱ፡፡ ግሪጎሪም መለሰና “ታዲያማ ትውልዱ ኹሉ በስሌት ተሳስተዋል፡፡ ያልተቈጠሩ እለታት አሉ” አለ፡፡ “ታዲያስ!” አሉት ደግመው፡፡ “ታዲያማ አሁን 532 ዓ.ም. አይደለም 7 ወይም 8 ዓመት ዘግይተናል፤ ፈጠን ልንል ይገባናል” አለ፡፡ ግሪጎሪም ለጠቅ አደረገና በዝርዝር የቀመሩን አካሄድና የስሕተቱን አፈጣጠር ሰፋ አድርጎ አስረዳ፡፡ ድምዳሜው ጠጠር ያለባቸው ጳጳሱም ጉዳዩንና ግሪጎሪን ይዘዋቸው የሮም ንጉሠ ነገሥት ዘንድ ቀረቡምና እዚያም ተብራርቶ እንዲቀርብ ተቀጥሮለት አቀረበው፡፡ 

ጳጳሱ የተገረሙትን ያክል ንጉሠ ነገሥቱም በአሳቡ እጅጉን ተደመመ፡፡ የሮም መንግሥትና የሮም ቤተ ክርስቲያን አመራሮችና አባቶች በአፋጣኝ በዓለም ዙሪያ ላሉ የንጉሠ ነገሥቱ ግዛቶች መልክት አስተላለፉና የጊዜ መቊጠሪያው በ7-8 ዓመታት እንዲሻሻል ትእዛዝ አሉ፡፡ ሮምን ትኩሳት ያዛት ዓለምም በረዶ መቸለስ ጀመረ፡፡ (ሲሠራበት የነበረው የጊዜ ቀመር ተተወና በ7-8 ዓመታት ተስተካክሎ መቈጠር ጀመረ፡፡)

ይህ ዜና ታዲያ ወደኢትዮጵያ ሲመጣ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ የያኔዋ ኢትዮጵያም ዓለም የጊዜ ቀመሩን እንዳሻሻለና እርሷም ይህኑ ልታደርግ እንደሚገባት መልእክት ደረሰ፡፡ 

በነገራችን ላይ እዚህ ጋር ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አንድ ነገር ልነገራችሁ እገደዳለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከጥንተ መሠረታቸው ጀምሮ የራሳቸውን የሕይወት ዘይቤና የራሳቸውን ፍልስፍና እየተከተሉ የሚኖሩ፤ በዚህም ረገድ በማንም እንግዳ ላይ ጥገኛ ያልሆኑ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ከልጅነታችን ጀምሮ “እንዲህ አለ እንዲያ ተነፈሰ” እየተባልን ቃሉን እንደወንጌል ቃል ደጋግመው ሲያስጠኑን የነበረው የጥንታዊት ግሪክ ዝነኛ ፈላስፋ ሆሜር ስለእነዚህ ሕዝቦች ኢሊያድና ኦዲሴ በተባሉት መጻሕፍቱ ይህን ተናገረ፡፡ “በዓለም ከሚኖር የሰው ዘር ኹሉ ኢትዮጵያውያን ርትዕ ያላቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡  በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣውና በእስልምና እምነትም ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነቢዩ መሐመድም “ኢትዮጵያውያን መሃል ማንም አይወነጀልም” ሲል ስለሕይወት ዘይቤአቸው ጠንከር ያሉ ምስክርነቶችን ሰጥቷል፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያውያን ነገርን ኹሉ እነርሱ ትክክለኛ በሚሉትና የሚያምኑበትን ነገር ይበልጥ በሚገልጥላቸው መልኩ ያከናውናሉ እንጂ ማንም ስላፏጨ የሚያጨበጭቡ ሕዝቦች አይደሉም፡፡ ከኹሉም በላይ ኢትዮጵያውያን ነገርን እንደዋዛ የሚቀይሩ ሳይኾኑ ኹሉን በምክንያት የሚመረምሩ ልባሞች ናቸው፡፡

የመነኩሴው ግሪጎሪ የሒሳብ ስሌት ታዲያ ከምድረ እስጳኝ እስከ ሩቅ ምሥራቅ፣ ከበላእያነ ሰብ (ራሽያ) በግብጽ በኩል እስከ ኑቢያ ያለውን የዓለም ሕዝብ ቀልብ ገዝቶ እርሱንም ሊቅ አስሰኘው፡፡ ያቺም መልእክት ኢትዮጵያ ምድር ስትዘልቅ ከምናከብራቸው ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ዘንድ ደርሳ ጠረጴዛቸው ላይ ለሂስ ተዘረጋች፡፡ ስታሳዝን፡፡ እንደዚህ ያለውን በእግዚአብሔር ጥበብ የሚኖርና ከፍተኛ የውስጥ ሰላምና ልበ ምሉዕነት ያለውን ኩሩ ሕዝብ ለማሳመን ያቺ መልእክት የሚደነቅ ርትዕ (Righteousness) ይጠበቅባት ነበር፡፡ ምክኒያቱም ኢትዮጵያውያን ዓለም ካወቀው ጥበብ ኹሉ ርቀው ሄደው ነገርን ኹሉ ማንም ካደረገው ተቃራኒ አድርገው ማንም ያላገኘውን የሚደነቅ ውጤት የሚያመጡ ትክክለኞች ሕዝቦች ነበሩና ነው፡፡ የቀረው ዓለም ሕንጻ ሊገነባ ሲፈልግ ጡብ በጡብ ላይ እየደረደረ ወደሰማይ በሚያንጽት በዚያ ዘመን ከክምር አለት አናት ላይ ቆመው ወደታች እየቦረቦሩ ላሊበላን ወደምድር ከርስ የገነቡ ሕዝቦች ናቸው፡፡ የአክሱም ሐውልት አጠራረቡ ከሕሊና በላይ ነው፡፡ ከእርሱም በላይ ደግሞ የቆመው ያለመሠረት ነው፡፡ በዚህ እስካሁን ድረስ በዓለም ያለው ትልቁ የጥርብ አለት ሐውልት ነው፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ሐውልቶቹ በንደዚህ ያለ ጥበብ ተፈልፍለው የተፈሸኑት አሁን ከቆሙበት ቦታ ቢያንስ 4 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ነው፡፡ ጎማ የሚባል አንዳችም ክብ ነገር ባልተፈለሰፈበት ዘመን እንደምን አድርገው ይህን ግዙፍ ቁስ አጓጉዘው እዚህ ተከሉት፤ የዘመናችን ጥበበኛ መልሱን ለማወቅ እየተጋለት ያለ ጥያቄ ነው፡፡ ከእዚህ ታላቅ ሕዝብ ዘንድ እንዲህ ያለ ትውልድን የሚኰንን የአንድ መነኩሴ መልእክት ከአውሮጳ ሲመጣ ታዲያ እንደሌላው ዓለም መነኩሴውን ለማስመስገን የኾነች ዓይነት ትንሽ ሞገስ ታስፈልገዋለች፡፡ 

ታሪካችንን እንቀጥል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ የመልክቱን ይዘት በጥንቃቄ ከተረዱ በኋላ የጊዜ ቀመሩ ተሳስቷል፤ ይሻሻል የሚል መኾኑን ሲያውቁ በቀጥታ የኖሩበትን የሥነ-ፈለክና የቀመረ-አዝማን ጥበብ ገለጡ፡፡ ከዚያ ምን ልበላችሁ - የበዓላትን አዋዋልና የአጽዋማትን አባባት፣ የአውራኅን አጠባብ፣ አበቅቴና መጥቅዕን ወደፊትም ወደኋላም እያሉ ቀመሩ፡፡ ሞኝ ሊሞክረው ወደማይቸለውና ጥበበኛ ብቻ እየቀዘፈ ሊወጣው በሚችለው በጥንታዊው የዘመናት የቀመር ባሕር (ባሕረ ሐሳብ) ውስጥ ዋኝተው ጨርሰው ሲመለሱ የመነኩሴው የግሪጎሪ መልእክት ጸጉሯ ቆሞ ጥላ የራቃት ምስኪን ኾነች፡፡ ሊቃውንቱ ቀና አሉና ለዓለም ይህን ከተቡ፡

“ዓለም ሆይ! ይበጀኛል ያልኸውን መምረጥ የአንተ ነው፡፡ እኛ በዚህ ነቀፋ የለንም፡፡ ይቅርታም እየጠየቅን የምናሳውቀው ቁም ነገር ቢኖር ግን ክርስቶስ የተወለደበት ዓመት ቢያንስ 7 ቢበዛ ደግሞ 8 ዓመት ያህል ተሳስቷል እንድንል የሚያስችል ምንም ስሕተት አላገኘንም፡፡ የጊዜ ቀመራችንም ስንቈጥርበት የኖርነው ያሃው የምታውቁት ነው፡፡ እንቀይረውም ዘንድ በቂ ሰበብ አላገኘንም፡፡ ከሰላምታ ጋር!”

አሉና የጊዜ ቀመራቸው ላይ ማሻሻያውን ሳያደርጉበት ቀጠሉ፡፡ ከዚያም እለት ጀምሮ የቀረው ዓለም በመነኩሴው ግሪጎሪ ስም "ግሪጎሪያን ካላንደር እያለ የአውሮጳውያኑን ባሕረ ሐሳብ ሲከተል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግን በቀደመው ዓለም አቀፋዊ የአቡሻኸር ቀመረ አዝማን ቀጠሉ፡፡ እነሆም 2007 ዓ.ም. ደረስን፡፡ 

ውድ ኢትዮጵያውያን! 

መነኩሴው ግሪጎሪ ትክክል ቢኾንና የተባለው ስሕተት ተሠርቶ ቢኾን ኖሮ በዚህ ይታወቅ ነበር፡፡ እስከ 532 ዓ.ም. ድረስ በተፈጠረው የአቈጣጠር ስሕተት ምክንያት የ7ና የ8 ዓመት ልዩነት ቢመጣ ኖሮ የኢትዮጵያ ቀመር በዚያው ቀጥሎ ልክ 1064 ዓ.ም. ላይ ሲደርስ ቀድሞ ተከሰተ የተባለው የ7ና 8 ዓመት ልዩነት በቀረ (በተቻቻለ) ነበር፡፡ ገፍተንበትም ልክ 1596 ዓ.ም. ላይ ስንደርስ የአቈጣጠር ስሕተቱን ሳናርመው ስምንሄድ ጎርጎሪዮሳዊውን የጊዜ ቀመር በ7ና በ8 ዓመት ጥለነው ወደፊት በከነፍን ነበር፡፡ በአጠቃላይም አሁን ባለንበት ዘመን ቢያንስ 14 ቢበዛ ደግሞ 16 ዓመት በቀደምናቸው ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም ግሪጎሪ ያስተካከላት 8 ዓመት ከነኩርፊያዋ ተቀምጣ በእኛና በእነርሱ መቊጠሪያዎች መካከል ያለች አጠያያቂ ልዩነት ኾና ቀርታለች፡፡ ይህ የሚያስረዳው ግሪጎሪ እንዳለው በቀድሞው የጊዜ ቀመር ስሌት ላይ ዓመታትን ወደኋላና ወደፊት የሚለጥጥና የሚስብ ስሕተት አለመፈጸሙን ነው፡፡ ይህን ታሪክ በስፋት ከዘገቡት መካከል ይህችን የቢቢሲ ዘገባ ያንብቡ::  

ይልቁኑ የሚገርመው ግን ልክ የዛሬ ዓመት 2006 ዓ.ም ተቀብለን እንቁጣጣሽን ካከበርን በኋላ በመጣው ረቡዕ እለት የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ቤኔዲክት 26 አዲስ መጽሐፍ አሳትመው አስመረቁ፡፡ ጳጳሱ በመጽሐፋቸው ውስጥ ሰፋ ያሉ ሥርዓታዊና ቤተ ክርስቲያናዊ ኹነቶችን የዳሰሱ ሲኾን አንደኛው ክርስቶስ ተወልዷል ተብሎ ከሚታሰብበት ዓመት 5 ዓመት በኋላ ተወልዶ ሊኾን እንደሚችልና የአሁኑ የጊዜ መቊጠሪያም 5 ዓመታትን ሳይፈጥን አይቀርም ብለው መጻፋቸውን የዓለም የመገናኛ ብዙኃን እየተቀባበሉ አወሩት፡፡ አንዱን እዚህ ሊያነቡት ይችላሉ (የዴይሊ ሜይል ዜና) በዚህም መነኩሴው ግሪጎሪን ስለሠራው ስሕተት ወቀሱት፡፡

የጳጳሱ ቤኔዲክት የአሁኑ ክስ ስለኢትዮጵያ ምንም ያለው ነገር ባይኖርምና ስሕተቱ የ7 ወይም 8 ዓመት ነው ባይልም ስሕተት እንዳለ ማመኑ ብቻ መነኩሴው ግሪጎሪ (ኢትዮጵያውያን ባወጡለት ስሙ ጎርጎርዮስ) የሠራውን ዝነኛ ስሕተት ያጎላልናል፡፡ 

እስኪ አሁን የቤተሰብ ጨዋታ ላጫውታችሁ፡፡ኹል ጊዜ ይህን ታሪክ ሳስብ አንድ ጥያቄ ውስጤን ሰንጥቆ ገብቶ አንጀቴን ያውስብኛል፡፡ ኢትዮጵያውያን የነበረን ያሃ ኹሉ በራስ መተማመንና ለራሳችን ያለን ክብር በዚህኛው ትውልድ የት ሄደ? ዛሬ የኢትዮጵያ ልጆች ለነጭና ነጭ ላጎበደደለት ነገር ኹሉ በርና መስኮታቸውን በጥድፊያ እየከፋፈቱ ይገኛሉ፡፡ ከአነጋገራችን (ቋንቋችን) አንሥቶ አጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤአችንና ለሕይወት የምንሰጠው ፍቺ ኹሉ በአስደናቂ ፍጥነት ምዕራባውያን “ነው!” ወዳሉት ነገር እየቀየርን እንገኛለን፡፡ በአሁኑ ሰዓት በዓለም ካሉ ኹሉ እንደሐበሻ ልጆች ሕይወትን ያወቀበት ፈረንጅ ነው ብሎ የሚያስብና አነጣጠስ አነፋፈጡን ሳይቀር ከእነርሱ እየኮረጀ ያለ ሌላ ተወዳዳሪ የለም፡፡ እኔን የሚገርመኝ ግን ካልጠፋ ዘር እንዴት ሐበሻ እንደዚህ ያስባል

እባካችሁ ኢትዮጵያውያን! ታሪክ እንዳንሰርዝ፡፡ የእኛ የኾኑትን እሴቶች ኹሉ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እንጠቀምባቸው፡፡ እንዲጠፉም አንፍቀድ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንድ ነው፡፡ የቀደሙ አባቶቻችን ከምናስበው በላይ ጥበበኞች ነበሩ፤ ነገርንም በጥሩ ምክንያት የሚያከናውኑ ነበሩ፡፡ ታዲያ እነርሱ ያወረሱንን እሴት እንደዋዛ ተነሥተን ስንሰርዘው ጥሩ ምክንያት ያስፈልገናል፡፡ እኔን ብትጠይቁኝ ግን ምንም ምክንያት ሊኖረን አይችልም ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ለእነዚህ ጥበበኛ ሕዝቦች የዘመናት ጠበብት እንኳን ጥሩ ምክንያት ሊያቀርቡላቸው አልቻሉም፡፡

ለአብነት ያህል ይህችን የጊዜ ቀመራችንን የትመጣ ላወቀ ሰው መቼም “ውይ! ዛሬ ቀን በሐበሻ ስንት ነበር! አይ የኔ ነገር፤ እኔኮ የሐበሻ ካላንደር ያን ያህልም ነኝ!” እያለ ጎረርኩ መስሎት የሚዘቅጠውን ወገኛ ያገሬን ሰው ማየት ክፉኛ ያተክነዋል፡፡ ፈረንጅ ባሞቀው ኹሉ እየገባን ማድመቅ ያለብን ከመሰለን ፈረንጅ ጭፍን ኹኖ የዘባረቀበት ቦታ ኹሉ ገብተን ልንዘባርቅ ነው፡፡ እንዴ! ፈረንጅምኮ ይሳሳታል፡፡ በርግጥ ከእነርሱ ጋር ለሚያገናኘን ጉዳይ ኹሉ ጎርጎርዮሳዊውን መቊጠሪያ መጠቀም ግንኙነቱን ያቀልልናል፡፡ ነገር ግን የልብስ ንጽሕና ሱቆች፣ ባንኮች፣ የገበያ ማዕከሎችና እኒህን የሚመስሉ ቦታዎች በምናደርገው የንግድም ኾነ ሌላ እንቅስቃሴ ቀን መጻፍ ግድ ሲለን የጎርጎርዮስ ባሕረ ሐሳብን የምንጽፍበት ቁራጭ ምክንያት የለንም፡፡ እኛ ከተውነው ግን ልጆቻችን ዓመት ዐውደ ዓመቱን ከየት አምጥተው ሊያከብሩት፡፡ ጎርጎርዮስ እንደሁ ለዚህ ስልት አላበጀለት፡፡ ክብር ለኢትዮጵያውያን አባቶች! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

Comment on this