ታዋቂ ልጥፎች

ገፆች

2014 ጁላይ 24, ሐሙስ

ሚስ! ... እባክሽን!





ለእርሷው ለእትዬ የተጻፈ የብሶት ደብዳቤ፡
ይድረስ ኹል ጊዜ ለማስብሽ፣ልጄንም ባየሁ ቊጥር ለምትታወሺኝ ለሚስ


ለጤናሽ እንደምን አለሽ፤ደኅና እንደኾንሽ እገምታለሁ፡፡

እኔ ይኸውልሽ የወላጅና መምህር የተግባቦት መጽሐፍ ላይ የተተወችልኝ ባለ አንድ መስመር አስተያየት መጻፊያ ቦታ ከፊርማ መፈረሚያ አልፋ የሠሙኑን ብሶቴን ለማውጣት አላስፈነጭህ ብትለኝ ጊዜ ደብዳቤ ጻፍኹ፡፡ አማርኛ ማንበብ እንደሚሰለችሽ እረዳዋለሁ፤ነገር ግን
እግዚአብሔር ረድቶኝ፣እንደኹ በሕይወት ዘመንሽ ለአንድ ጊዜ ብቻ ቅን ብትኾኚ፣ማንነት ቢገድሽና ጨክነሽ ብታነቢልኝ ብዬ ነው፡፡

ሠሙኑን ትንሽ ጤናዬን አጥቸ ቈየሁ፡፡ በሰበብ አስባቡ መቈጣት ሰነበተብኝ፡፡ ምናልባት ክፉ መንፈስ ይዞኝ እንደኾን ብየ ጠበል ሄጄ ነበር፤ሰላም ነው፡፡ ሰንብቼ ግን ደርሸበታለሁ፡፡ የልጄ ስብእናው ተለውጦ ነገረ ሥራው ኹሉ እንደ ምዕራባውያን መኾን ትንሽ ያስደነገጠኝ ይመስለኛል፡፡ በቀደም እለት በሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ያዘጋጀነውን ጸዲቅ ጸዲቅነቱን እየነገርን ክቡር እንደኾነ ብናስታውቀውም እርሱ ግን በማርጋሪን እየለወሰ አወራረደው፡፡ ለፋሲካ ዋዜማ ሊቀቀል የተዘጋጀውን እንቊላል ማንም ሳያየው በባለቀለም ብዕር ዐይንና አፍንጫ ጆሮና ጥርስ እየሠራበት አስጌጠው፤ብንቈጣው ለፋሲካ እኮ ወጉ እንዲህ ነው እያለ ሞገተን፡፡  

ሚስ! መቼም ለፋሲካ በዓል እንቊላል መቀባትን የምሥራቃውያን ባሕል ለልጄ እንዳላስተማርሽ ዐውቃለሁ፡፡ ቢኾንም ግን ልጄ የአገሩን ወግ ክፉኛ ጠልቶ በምዕራባውያኑ ፍቅር ክፉኛ እንዲነደፍ ያደረገው ነገር እኔን እንደሚመስለኝ ባለማስተዋል በተግባር ይህንኑ ስላሳየሽው ነው፡፡ ከአቡጊዳ አቅድመሽ ኤ ፎር አፕልን ነገርሽው፤አማርኛ በአንደበቱ እልፍ ቢል ቡሃቃ እንደገባ ውሻ እያደናበርሽ አስተዳዳሪው ቢሮ ገተርሽው፡፡ አማርኛን እርግፍ አድርጎ ትቶ በእንግሊዝኛ ሲኮላተፍ ሲውል ተደስታችሁ ምርጥ እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሚል ብጫቂ ወረቀት ሸለማችሁት፡፡ ይኼኔ ልጄ ኢትዮጵያና ጓዝ ጉዝጓዟ ኹሉ ኃጢአት ታላቋ ብሪታንያና ጓዟ ጉዝጓዟ ኹሉ ጽድቅ እንደኾኑ ተማረ፡፡ ሰው ማለት ለሱ ኒል አርምስትሮንግ፣አልበርት አንስታይንና ጆን ጉተንበርግ ናቸው፡፡ እንዳንቺ ቀለም የበቃውና ትውልድን የሚያንጽ ምሁር ሚስ እየተባለ በባሕርማዶው ልሳን እየተሞካሸ ሲጠራ እንደ ምስኪኗ እምዬ አይነቱ መሠረተ ትምህርት ያቋረጠና ቀለም የተሰወረው ደግሞ የሚጠራው በአገርኛው እትዬ እየተባለ እንደኾነ ሲያውቅ አገርኛውን ንቆ ባሕር ማዶውን ጠነቀቀ፡፡ እንዴት ብዬ ልፍረድበት፤አንድ ቀን እለት ስታድግ ምን መኾን ነው የምትፈልግ ብየ ጠየቅኹት፡፡ ብዙም ሳያሰላስል ኢንጂነር መኾን እንደሚፈልግ ነገረኝ፡፡ መሐንዲስ መኾንስ አትፈልግም ብዬ ብፈትነው ንክች አላደርገውም አለኝ፡፡ በአማርኛ ሲተረጎምበት ጊዜ ኢንጂነርን ጠራቢ አድርጎ ተረዳው፡

ሚስ! እባክሽን ስለእነ አሌክሳንደር ዘግሬት ስትናገሪ ለጥቀሽ ስለ እምዬ ምኒልክ ስለ ሕንደኬ ንግሥት ንገሪልኝ፡፡ እርሳቸውኮ አውሮጳዊ ሳይኾኑ አውሮጳዊን ወራሪ ኃይል ቆልተው ከአገራቸው ያባራሩ በዓለም የመጀመሪያ ናቸው፡፡ ስለእነ ኒኮላስ ኮፐርኒከስ ስትናገሪ ለጥቀሽ ስለበላይ ዘለቀ፣ባልቻ አባ ነፍሶ፣አሉላ አባ ነጋ ጨምረሽ ንገሪልኝ፡፡ አዎና! ጥይት እንግዳ ነገር በኾነበት ዘመን ደረታቸውን ሰጥተውት፣ትቢያ ላይ ወድቀው ያቆሙት እነርሱ እንደኾኑ ይወቅልኝ፡፡ ትግሬ ሲነካ እምቢኝ ያለው ጎጃሜ፣ኦጋዴን ስትነካ እኔ በሕይወት ቆሜ ያለው ወለጌ፣አድዋ ስትደፈር ዐይኔ አያይም ያለው ሸዋዬ እንደኾነ ይወቅልኝ፡፡  መቼም እኒህን ጀግኖች ሳነሣብሽ ምን ነክቶት ነው የጦረኛ መአት የሚጠራብኝ ብለሽ ልትታዘቢኝ እንደምትችዪ እገምታለሁ፡፡ ስለዚህ ሳትረሺ ደግሞ አክሱምን ያቆመ፣ላሊበላን የፈለፈለ፣ሐረርን ያጠረ፣ጅማን የቆረቆረ ጀግና አባት እንዳለው ንገሪልኝ፡፡ ይህን ስትሰሚ ደግሞ ምን ኾኖ ነው የአናጢ መአት የሚደረድርብኝ እንደምትዪ ይሰማኛል፡፡ ሚስ ግድ የለሽም ስለእነርሱ ንገሪልኝ፤እኔ ደግሞ በበኩሌ ስለ ካሌብና ዘርዓ ያዕቆብ፣አቡነ ተክለሃይማኖትና አላኒቆስ፣እስትንፋሰ ክርስቶስና ጊዮርጊስ ዘጋሰጫ እየነገርሁ ሙሉ ሰው አደርገዋለሁ፡፡

ሚስ! እስኪ እንደሁ ከልጄ ትክሻ ላፍታ ወረድ ልበልና ለመኾኑ ከስም ኹሉ መርጠሽ ሚስ መባሉን ስለምን ወደድሽው፤ድሮ ድሮ ዜማ የሚሉትና ቅኔ የሚፈቱት ሊቁ ኢትዮጵያዊ የቀለም ገበሬ መምሬ! የኔታ! እየተባሉ ይጠሩ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ አስኳላ የሚያስተምሩት ኹሉ ጋሸዬ እየተባሉ ይሞካሹና ይታፈሩም እንደነበር ዐውቃለሁ፡፡ አንቺ ስትመጪ ድንገት በእንግዶች ልሳን ሚስ በሉኝ አልሽ፡፡ ሆሄያቱ ሁለት ኾነው ቀለሉንና ተወጣነው እንጂ ትንሽ ደስ የማይል ትብብር ነበር የጠየቅሽን፤አዎና ከምዕራብ ሸዋ ተከርብተሽ በአንዴ ዌስት ኮስት? እሺ እንደሁ ፍቺውን ለኔ መንገሩን ተዪውና በቃ ፍቀጂልኝ፤እኔ እትዬ ልበልሽ፡፡ የኹለቱም ትርጉማቸው አንድ ከመኾኑ ባሻገር እንደዚህ ስልሽ የማላውቀው የኾነ አይነት የኩራት ስሜት ውስጤ ይመላለሳል፡

እና ይኸውልሽ እትዬ! ምን ይኹን ብለሽ ነው በቀደም እለት ያችን የምታክል ብጫቂ ጨርቅ አገልድመሽ ትምህርት ቤት ልታስተምሪ የመጣሽው፤ለብሰሽው ያየንሽ ወላጆች ቀሚስ መኾኑን ያወቅነው ሲነግሩን ነበር፡፡ እንደውም ከመሃላችን ወገብ ላይ የሚታሰር ወፍራም የጨርቅ ቀበቶ ነው ከሚሉ ጋር የጠና ሙግት ይዘን ነበር፡፡ እኔ የተሰለፍሁበት ጎራ በበኩሉ ቀበቶ የሚታሰረው ሱሪ ላይ አሊያም ቀሚስ ላይ እንጂ ባዶ ጭን ላይ አይለም በማለቱ ረታን፡፡ ያም ኾነ ይህ ልጄ እንዴት ያለ ቁም ነገር ይማር ብየ አንቺ አለሽበት ልስደደው፡፡ ደግሞ የገረመኝ በአለባበስሽ ደንግጨ ምናለ! እንደለመድነው እንደአገርኛው ሞላ ያለ ልብስ ብትለብሺ ብዬ ስጠይቅሽ፤አንቺም ሳትሳቀቂ ይሄምኮ ባሕላችን ነው፤አላየህም እንዴ ሐመር ውስጥኮ ብጫቂ የፍየል ቆዳ ነው የሚያገለድሙት፤ከዛ የተወሰደ ነው ብለሽ ቀለድሽብኝ፡፡ እትይ! ቀልደሽ ሞተሻል፡፡ ምን አሳብ እንደመጣልኝ ታውቂያለሽ፤በቃ ኮንሶ፣ጋርዱላ ውስጥምኮ ምንም አይለብሱም፤አፈርና ቀለም ብቻ ነው የሚቀባቡት፤ስለዚህ በቃ ልብሱን እንተወዋ፡፡ ይህ አባባልሽ አስደንግጦኝ አሥራ አንድ ቀን ተእኩል አንደበቴ ተዘግቶ እህልም ባፌ ሳይዞር በእውኔ ሳይኾን በሕልሜ መስሎኝ ሰነበትሁ፡፡


እትይ! ልጅ ተማረ የሚባለው እንግሊዝኛ አቀላጥፎ ስለተናገረ አይደለም፡፡ የኛ ትውልድ እንደምታውቂው መሃይም ትውልድ ነበር፡፡ እኔ በበኩሌ ነገር ቶሎ አይገባኝም፤ሳይንስም አልጠነቅቅም፡፡ እንደአያያዛችሁ ከኾነ ግን የእኔ ስጋት የሚቀጥለውም ትውልድ እንዲያው ነው፤የሚለየው እንግሊዝኛ ተናጋሪ መሃይም ስለሚኾን ይመስለኛል፡፡ ሳይንሱን ባግባቡ ሳታስጨብጡት ሙሉ ቀን አፉን አጣሞ ሲኮላተፍ ስለዋለ ትልቁ ዕውቀት እርሱ ነው የሚል ትዝብትን ለልጄ መስጠታችሁ ቀኖቼን እያበላሸብኝ ነው፡፡ እንግሊዝኛውን ይልመድልኝ፤ምን አስመቀኘኝ፡፡ ለእሱ የሚኾን እንግሊዝኛ እኔም አላጣም፤ነገር ግን አማርኛውንም ደግሞ ይልመድ፡፡ እንደውም እርሱን ያቅድምልኝ፡፡ አውሮጳውያን ተርበው በጨለማ ሳሉ የእኔ አባቶች ብራና ዳምጠው ቀለም በጥብጠው እምነትና ፍልስፍናን ይከትቡበት የነበረውን ኩሩውን ልሳን ይወቅልኝ፡፡

ማስተማር ካልቻልሽ ግን ቢያንስ ቢያንስ እኔ ሳስተምረው በጀ እንዲለኝ እንግሊዝኛ የመግባባት ጉዳይ እንደኾነና አማርኛ ግን የመግባባትም የማንነትም ጉዳይ እንደኾነ ንገሪልኝ፡፡ ፈርዶበት አንቺን ይሰማሻልና፤አንቺ የተናገርሽውም ኹሉ የሰማይና የምድሩ የመጨረሻ እውነት እንደኾነ አድርጎ ይቀበላል፡፡ በዚህ እኔ አልቃወምም፤ምክንያቱም አንድ ትውልድ መምህሩን ካላመነ አይቀጥልምና፡፡ ነገር ግን የእኔ ልጅ ባሰ፡፡ ነገር ኹሉ አንቺ እንዳደረግሽው ኾኖ ካልተደገመለት ይኰንናል፡፡ ጭራሽ በቀደመ እለት እናቱ አስነጠሰች፡፡ ከዚያም ንጥሻዋ በጣም ዝግ ያለ ኾኖ ከመለስተኛ ኩርፊያ ጋር የተስተካከለ ቢኾንበት ጊዜ ተቀየመ፡፡ ምነው ብለን ብንጠይቀው ሚስ ግን እንደዚ አይደለም የምታስነጥሰው አለን፡፡ እሷ እንዴት ነው የምታስነጥሰው ብለን ብንጠይቀው ጫን አድርጋ ነው፤ … ጮክ ብላ ነው የምታስነጥሰው አለን፡፡ ትንሽ ቆየና እኔኑ ንጥሻ መጥቶብኝ ለወንዶች በሚገባ ደንብ ጮክ ብዬ ጣራና ግድግዳው እስኪታወክ ሳስነጥስ ልጄ ጠቋሚ ጣቱን አንሥቶ እ…ንደሱ! አለኝና አረፈው፡፡ እትይ! ይህን ያክል የሚሰማሽ ከኾነ ብዙ የምትነግሪልኝ ነገር አለና በጀ በዪኝ፡


 የወላጅ ሚና ከፍተኛ ነው እንዳትዪን፡፡ ያንቺ ሚና ነው ከፍተኛ፡፡ ልጄ ካንቺ ጋር ይውላል ከእኔ ጋር ያድራል፡፡ ቀለም የሚቆጥርበትና ያወቀውን ኹሉ ያወቀበትን እለቱን አንቺው አንጪው፡፡ 

አገሬ ኢትዮጵያ ነገ ትልቅ አገር ትኾንልኛለች፡፡ የቀደመ ክብሯም በውድ ልጆቿ ይመለሳል፡፡ እርሷም ለዓለም ኹሉ በክብር ትታያለች፡፡ ይህ ሲኾን ግን ለሺዎች ዘመናት አባቶቼ ሲሠሩ ከኖሩት ታሪክና ማንነት ጋር እንጂ ከዚያም ከዚህም ተሰባስቦ ከተጣጣፈ አርቴፊሻል ፈረንጅነት (በግድ ካልፈረነጅኩ ባይነት) ጋር አይደለም፡፡ ልጄም የአባቶቼን አሻራ ሳይተው የፈረንጆቹን ልሳን በብቃት እየተገለገለበት በአማርኛውም እየተራቀቀበት እንዲያድግ ያስፈልጋል፡፡  

“ሺህ ዘመን የኖረ መሬት ዕድሜውን መግለጥና ያሳለፈውን ክፉ ደግ መተረክ የሚችልን ቅርስ ጥሎ ሌሎች የጣፉትን አይደርትም፤በሌሎች ለማማር አይጥርም፡፡ እንግዳን ማክበር እንጂ ለእንግዳ መሽሸጥ አባቶቻችን አላስተማሩንም፤ክብር ይግባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ፊደል አንድም መግባቢያችን አንድም ማንነታችን ነው፡፡ የፈረንጅ ልሳን ግን መግባቢያችን ብቻ፡፡ በመሠረቱ ታሪክ ዳቦ አይኾንም የሚል ተከራካሪ ሊኖር ይችላል፤በርግጥም አዲስ ታሪክ መሥራት ከኹሉ ይበልጣል፡፡ ኾኖም ግን ታሪክ ለመሥራት ታሪክን መሰረዝ ቅድመ ኹኔታ አይደለም፡፡ ታሪክን ጠብቆ አዲስ ታሪክ መጨመር ባለኹለት ዲናር ያደርጋል፡፡ ከሌላ የሚኮርጅ ኹል ጊዜ የተናቀ ነው፤የራሱን ዘይቤ የሚከተልና ለሕይወት የራሱ የኾነ ፍች ያለው ሕዝብ ግን ይታፈራል፤ይከበራል፡፡ በተለይ ደግሞ ጥቁሮች የራሳቸው ምንም የሌላቸውና መሠልጠንን ገና ከምዕራባውያን የሚጠብቁ ተደርገው በሚታሰቡበት ዘመን ለዚህ አስተሳሰብ የሚሽሩ ማስረጃዎች ያሏት ብቸኛ! ጥንታዊት አገር ኢትዮጵያ ናት፡፡”

ያንቺው!!!

Comment on this