ታዋቂ ልጥፎች

ገፆች

2014 ጁላይ 24, ሐሙስ

የወራሽ ያለህ!!!



እናንተዬ! እንዴት ጭንቅ ብሎኛል መሰላችሁ፡፡ እንደሁ የ፳ኤል ቅዱስ መላ ይጠቁመኝ እንጂ ምን እላለሁ፡፡ እምላችሁ! እንዲህ እንደኔ ጭንቅ ሲላችሁ ምንድን ነው የምታደርጉት፤ አንዳንዶች ያንጎራጉራሉ፣ይቀኛሉ፣ሌሎች ስንኝ ይቋጥራሉ፡፡ እስቲ ቆይ ስንኝ ልቋጥር፡፡ … እንደውም ለምን እቋጥራለሁ፤በቀደም ለት በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የገጠመኝን አንድ ግጥም ልበልላችሁና ብሶቴን ልወጣ፡፡ አብዲ ሰኢድ ነው አዋሳ ኾኖ በኹለት ሺህ ዓ.ም. ለአቢቲ የላከለት፡፡



ሀ - ሁ … አ - ቡ - ጊ - ዳ
ገና ከማለዳ ልጅነቴን ለምዳ፣
ከስትንፋስ ከደሜ ከነፍሴ ተዋህዳ፣
ሀ - ግእዝ … ሁ - ካዕብ
ሂ - ሳልስ … ሃ - ራብዕ
ሄ - ሃምስ … ህ ሳድስ …
በዜማ ስለቅም በኅብር ሳወድስ፣
መልእክተ ዮሐንስ መልእክተ ዮሐንስ፣
ስከልስ ስከልስ ለነፍሴ ሳሠልስ፣
በአገራዊ ቃና
ሕይወቴ እንዲቃና
የኔነት እኔነት በደሜ እንዲዘራ፣
የኔታ በኩርኩም አባም በከዘራ፣
የለፉልኝ እኔ ያደግሁት ልጃቸው…
…ዛሬ ወጉ ደርሶኝ አባት ኾኜላቸው፣
ልጄን ከቀለም ቤት በኩራት ሰድጄ፣
አቡጊዳም እዳ፣
እኔነትም ባዳ፣
ኾኖበት ሲቸገር አይቼ ነድጄ፣
እንደተብከነከንኩ … !
እንደተብሰለሰልኩ … !
ኤ ፎር አፕል ብሎ ልጄ አፉን ፈታ፤
ኤን ብቻ! የምትሰብክ ከፊደል ገበታ፣
ግእዝ የማታዜም ቅኔ የማትፈታ፣
ማንነት ማይገዳት የማትሰጠው ቦታ፣
ሚስ ናት የሱ የኔታ ሚስ ናት የሱ የኔታ፡፡

እሰይ አብዲ! እንደው ብሶቴን ኹሉ አወጣኽልኝ! ከእለታት በአንዱ ካንዲካ የምትባል ፖላንዳዊት የሥራ ባልደረባዬ አዲሳባን በእግር በመጓዝ ልታያት እንደፈለገችና አብሬአት ብጓዝ ደስ እንደምትሰኝ ነገረችኝ፡፡ እኔም አገሬን በጣም የምወድና በተለያየ መልኩ ሊመረምሯት የሚሹ እንግዶችን በምችለው ኹሉ ማገዝ የሚያስደስተኝ ስለኾነ ፈጥኜ ፈቃደኝነቴን ገለጥኩና ተያይዘን መዞር ገባን፡፡
እናንተ! ለካስ አዲሳባ ለእንግዶች አይደለም ለቤተኞች  የሚኾን አንዳች ጥሪት የላትምና!

እጅግ የተጐሳቈሉ አረጋውያን በቀረቻቸው ጕልበት ተስበው መጥተው ካንዲን በመማጠን ገንዘብ ሲለምኗት፣ ‘አይ ይህቺን እንኳን በሲ.ኤን.ኤን. ዘጋቢ ፊልሞች ላይ ሳታይ አትቀርምና ብዙም አትደነግጥም ’ አልኩ፡፡ ሕፃናቱም የሚያውቁትን ኹሉ እንግሊዘኛ እየገጣጠሙ ዳቦ ሲጠይቋት፣ ‘ይህችም ብትኾን ከቢ.ቢ.ሲ. መቅረፀ-ምስል ያለፈች አይመስለኝም ’ አልኩ፡፡ ካንዲ ግን ያኔ በ፲፱፻፸ዎቹ አቅም አንሶት በረሃብ እመሬት ወድቆ በንሥር ሲበላ በትርእይተ መስኰት ያየችው ሕፃን ብርታት አግኝቶ መጥቶ ዳቦ የለመናት እስኪመስላት ተሳቀቀች፡፡ በመንገድ ላይ አካላቸው የጐደለባቸው ሰዎች የሚያሰቅቅ ቊስላቸውን ለሕዝብ እይታ ግልጥ አድርገው ሲለምኑ የካንዲ መሳቀቅና የአገሬ መቅለል ኹለት ኾነውብኝ አደረቁኝ፡፡ በግንባታ ሥራዎች ውል ዓለሙ የጠፋባቸው መንገዶችን ስናይ አዲስ አበባችን ቆሻሻዋን ማንም ሊያነሣላት ፈቃደኛ ያልኾነ ምስኪን ኾነችብን፡፡ ድንገት ንጹሕ ልብስ የለበሰች ጉብል ካንዲ ተመለከተችና ኢትዮጵያውያን ከአውሮጳውያን ይልቅ አሥር እጥፍ የምንበልጥ ፋሽን ተከታዮች መኾናችንን እንደታዘበች ልትነግረኝ ገና አፏን ስታላቅ የአገሩን ጉድ የጫኑት የሚመስል አይሱዙ መጥቶ በጥንድ ጎማዎቹ ቀይ አፈር የበጠበጠ ቊጥር ውኋ አንሥቶ ወጣቷን አልብሷት የተለመደ ሕይወቱን ቀጠለ፡፡


ይህን ኹሉ ትርእይት ሳይ ለካንዲ ልተርክላት የነበረውን የሦስት ሺህ ዘመናት ታሪክና ቅርሳችንን ተውኩትና ወኔ በማጣት ስሜት ስለአገራችን የታዘበችውን ነገር እንድትነግረኝ ጠየቅኋት፡፡ ፊቷን ጨምደድ አድርጋ፤ “ውሸት ብነግርህ ስለማይጠቅምህ ግልፅ ልኹንልህና አገራችሁ ገና በንብርክክ የምትሄድ ደኻ አገር ናት” አለችኝ፡፡
ሕሊናዬ  ቅን ስለኾነችልኝ ካንዲን አመሰገናት፡፡ ለጠቅ አደረገችና “ነገር ግን ብዙ የውጭ ዜጎች ያረጋገጡልኝና እኔም የታዘብኩት ነገር ኢትዮጵያውያን ጥንታዊ ማንነታቸውን ያልለቀቁና ስብእናቸውን የሚጠብቁ በአገራቸው ላይ ታላቅ ኩራትና ትምክህት ያላቸው ሕዝቦች መኾናቸውን ነው፤በዚህ ምክንያት ከዚህች አገር ጋር በፍቅር የወደቁ ብዙዎችን አውቃለሁ” አለችኝ፡፡

ጎሽ! እንዲህ ያሉትን ሰዎች እኔም ስለማውቅ ደስ አለኝና በቃ ስለጥንታዊ የብራና ጽሑፎቻችንና የራሳችን የፊደል ሥርዓት እንዳለን ልንገራት ብዬ መራቄን ስውጥ ዙሪያዬን የከበቡኝን ፎቆች ፊታቸውን ኮሶ አስመሰሉና አፍህን ያዝ አሉኝ፡፡ ካፒታል ገስት ሃውስ፣ዜድ ታወር፣ዜብራ ስቴሽነሪ፣ኢንፎርመር ጋዜጣ ኒውስ ፔፐር፣ባርክሌይስ ኢንተርኔት ካፌ፣ዳይናሚክ ላውንደሪ፡፡ ላፍታ ዝም አልኩና ምናለበት ሳዱላ የእንግዶች ማረፊያ፣ዘውድ ማማ፣ብራና የጽሕፈት መሣሪያ መደብር፣ራዕይ ጋዜጣ፣ዋሊያ ኢንተርኔት አገልግሎት ወዘተ. እያሉ ቢሰይሟቸው


አማርኛን! ያገሬን ልጅ በአገሬ ምድር አማትሬ ባጣው ግዜ ስለኢትዮጵያ ላወራው የፈለግሁትን ታሪክ ኹሉ የማያት አዲሳባ የመደገፍ አቅሙም ፍላጎቱም እንደሌላት አየሁ፡፡ ሀብታም ነን እንዳልል ድህነታችን አውራ ጎዳናዎቻችን ላይ ፍስስ ብሎልናል፡፡ ታሪካችንን እንዳልተርክ የማየው ከተማ የምዕራባውያንን ድሪቶ የደረተና የሆሄ ሥርዓት ባልጠበቁ የእንግሊዝኛ ቃላት የተጣጣፈ ከተማ ነው፡፡ ታዲያ ምን ቀረን አልኩ በልቤ፡፡ ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች አገር እንደኾች ደስ በሚል አተራረክ ልተርክላት ፈለኩና ደቡብ አፍሪካን ቅኝ የገዛች ማን እንደኾነች ጠየኳት፡፡ ፈጠን ብላ እንግሊዝ አለችኝ፡፡ ዚምባበዌ፣ሞሮኮ፣ዛንዚባር፣ሌሶቶ፣ሴኔጋል … ኹሉንም ሳትሳሳት መለሰችልኝ፡፡ መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያስ አልኳት፡፡ በጣም ጥቂት አሰብ አደረገችና በርግጠኝነት እንኳ እንደማታውቅ ነገር ግን እንግሊዝ ብላ እንደምትገምት ነገረችኝ፡፡ ያን ጊዜ የታሪኬን ሴራና የግጭቶች ጡዘት ረሳሁና እንግሊዝ ያለችው ቀልቤን ያዘው፡፡ 
ወገኖቼ! ልብ ብላችሁ ከተማችንን ተመልከቷት፤ትውልዱ መናገር የሚፈልገው እንግሊዝኛ፣የሚጽፈው እንግሊዝኛ፣ቀን የሚቈጥረው በጎርጎርዮስ፣የሚከበረው በእንግሊዝኛ፣የሚናቀውም በእንግሊዝኛ፣ሱቁ፣ሆቴሉ፣የገበያ አዳራሹ … ኹሉም እንግሊዝኛ፡፡  ይኼኔ ቅድም ድኾች ናችሁ ስትለኝ የተሰማኝ ዓይነት ነዘርዛሪ ጥፊን የሚመስል ሌላ ጥፊ ተጨመረልኝ፡፡ እነ ጁቬንቱስ ፀጉር ቤት፣ኤም.ዲ. ሚኒ ማርኬት፣ለንደን ካፌና ማክስ ኦዲዮ ቪዲዮ በዓይኔ ላይ ብልጭልጭልጭ አሉብኝ፡፡ ከጓደኞቼ መካከል በቅጽል ስማቸው ዛክ የተባለው ሕዝቅኤል፣ቤቢማን የተባለው አበበ፣ኤዲ የተባለው አዱኛ፣ዲቢ የተባለችው ድርቤ ታወሱኝና አይ ማንነት አልኩ፡፡ ልጆች እያለን የኔታ ትምህርት ቤት ተሰብስበን አቡጊዳን ስንቈጥር የነበረው ትርእይት ዘመን ተቀይሮ ኤ ፎር አፕል፣ቢ ፎር ባናና ከሚሉት የማውንቴን ሳይድ አካደሚ ሕፃናት ድምፅ ጋር ሲቀላቀልብኝ ትኩሳት አስያዘኝ፡፡ ካንዲ አዲሳባ ውስጥ ሁለት ሳምንት ብትቈይ ያስቀረችልንን የመጨረሻዋን ትምክህት በደማቁ ቀለም አጥፍታ ያለስም ትታን እንደምትሄድ ገባኝ፡፡


ከእለታት በአንዱ የትርእይተ መስኮቴን ጣቢያ አንድ ኢትዮጵያዊ ጣቢያ ላይ ቀስሬ መርሐ ግብሮቹን ስከታተል ጋዜጠኞቹ የሚናገሩት ወሬ ኹሉ አንድ ቋንቋ ብቻ አለመኾኑንና ይህም ወደው ያደረጉት እንዳልኾነ ተረዳሁ፡፡ እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገራቸው በሦስት መናኛ መናኛ የኾኑ የአማርኛ ቃላትና በኹለት የሚጠበዳድሉ እንግሊዘኛዎች የተዋቀሩ ጉራማይሌ መኾናቸውን ተመለከትሁ፡፡ እንደነገሩ ቢኾን ኖሮ ኮሌጅ ድረስ በመድረሴ የቈጠርኋትን ቀለም አመስግኘ ማለፍ ነበረብኝ፡፡ ቅሉ እኔ ኮሌጅ እንድጨርስ ከአምስተኛ ክፍል መሠረተ ትምህርት አቋርጣ አቧራ አቡና ያለአባት ያስተማረችኝ እናቴስ ጋቢ ለብሳ ከሚባለው ነገር ውስጥ ነጥብ ለመያዝ ስትዳክር ሳይ ምን ላድርግ፡፡ አይ ትውልድ! መሬት ፍቀው ያስተማሩትን ቀደምቶቹን ጣት የሚነክስ ውለታ በል! እፊት ለፊቴ ተቀምጣ የበቆሎ ቅቅል ትግጥ የነበረችው የስድስት ዓመቷን የወንድሜ ልጅ የጋዜጠኞቹ ብሂል ምን ማለት መኾኑን ካወቀች ብዬ በፈተንኋት ፈተና እንግሊዘኛውን እየፈታች አብጠርጥራ በምሳሌ ጭምር ስታስረዳኝ ግዜ ተገረምሁባት፡፡ ወዲያውም እየበላች ያለችው ነገር ምን መኾኑን ጠየቅኋት፤
ይህማ ቀላል ነው አጎቴ!
“ንገሪኛ!”
“‘ሜይዝ’ ነው”
“ምን፤”
“ሜይዝ”
እርሱ እንግሊዘኛ ነው በአማርኛ ንገሪኝ ” 
ልጅቷ ሊተኩስ እንዳነጣጠረ ሰው ቀኝ ዓይኗን ሸውረር አድርጋ ግራ በመጋባት ትክ ብላ ተመለከተችኝና በአማርኛ ሰምታው እንደማታውቅ ነገረችኝ፡፡ እኔም አባዜዬ ተነሥቶብኝ
እንዴት የአገርሽን ቋንቋ አታውቂም! ይሄኮ ማንነትሽ ጭምር ነው” ብዬ ተናገርሁ፤
ወዲያው በአሳቤ የኔታን ፈንግላ በመንበራቸው የተደላደለችው “ሚስ”ትዝ አለችኝና ሕፃኗ ላይ መፍረድ ተውኩ፡፡ ለሰዓታት ይህ ከሕሊናዬ ሳይወጣ “አይ እምዬ ኢትዮጵያ! እኔም አንቺም ውኃ በላን” እያልኩ የትውልድን ነገር እያሰላሰልኩ ካለሁበት ሕፃኗ ጠራችኝ፤
አጎቴ ይቅርታ ቅድም ትዝ ስላላለኝ ነው፤ስበላ የነበረው ‘ኮርን’ ነው” አለችኝ፤
”ምንድን ነው፤”
“‘ኮርን’“
ሌላ እንግሊዝኛ፡፡
ትኩር ብዬ በደምብ ሳያት ትኩር ብላ በጕጕት አየችኝ፡፡ ይህች የስድስት ዓመት ሕፃን ስትበላ የነበረውን ነገር በኹለት የእንግሊዝኛ ቃላት መግለጥ ስትችል በአንድም አማርኛ ልትጠራው ግን አትችልም፡፡ ከዚያም “ግድ የለም እናቴ! ያንቺ ጥፋት አይደለም” ብዬ እርሱንና ሌላም አማርኛ ጨመርመር አድርጌ አስጠንቼ መለስኳት፡፡ እኛን ለሚከተለን ትውልድ አማርኛ ትንግርት እንደሚኾንበትና የአማርኛ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍን ረስታችሁት መግባባት እንኳ ብርቅ እንደሚኾን ስተነብይ ልቤ በኃዘን ጉዳት ኾኖብኝ ነው፡፡ 

አንድ ሠሙን አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ የምግብ አዳራሽ/ሬስቶራንት በር አፍ ሳገድም የታዘብኩት ልንገርና ላብቃ፡፡ ቤቱ ባለመዓርግ ከመኾኑ የተነሣ የተመረጡ ሰዎች የሚገለገሉበት ነው አሉ፡፡ ታዲያ ይኸው ቤት ጥሬ ሥጋ እንደሚሸጥ የሚነግር ጉልህ ማሳወቂያ ለጥፎ በእንግሊዝኛም ተርጕሞ ጽፏል፡፡ ይኼኔ “ጥሬ ሥጋ” ለሚለው “ራው ሚት” ብሎ ሲጽፍ “ሚት” ያለውን ግን የጻፈ በጥንድ ኢ (ደብል ኢ) ነበር (“ሚት” በጥንድ ኢ ሲጻፍ “ስብሰባ” ማለት እንጂ “ሥጋ” ማለት አይወጣውም፡፡) ግራ ተጋባሁና በሆዴ እሪሪሪ በል! ጥሬ ሥጋ …. ጥሬ ስብሰባ! … በሌላም ቦታ “ሜሪ ክሪስማስ” ሊል (ገጽ በገጽ መልካም የክርስቶስ ልደት ማለቱ ነው፤በላቲን ቋንቋ) ሜሪን በኤ ጻፈ (ሜሪ በኤ ሲጻፍ “ማርያም” ማለት እንጂ “መልካም” ማለት አይኾንም) ክሪስማስን ደግሞ “ቲ”ን ሳያካት ጻፈ (ቲ ካልተካተተ የክርስቶስ ልደት ሳይኾን የሌላ “ክሪስ” የሚባል ሰው ልደት ኾኖ ያበላሻል፡፡)

ወገኖቼ! የዚህ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ዐቃቢያን ኢትዮጵያውያን አበው ነበሩ፡፡ በዘመናት ኹሉ የሥልጣኔ አውራዎች ኾነው ትውፊቱን ሊያጠፋው ያለውን ኹሉ እየተከላከሉ እዚህ አድርሰዋል፡፡ ዛሬም ቢኾን በምዕራባዊነት ደመና መቅዘፍ የሚፈልግ ይህን ረጋ ሠራሽ ትውልድ ልቡን መመለስ የኛ የልጆቻቸው ድርሻ ነው፡፡ ልጆቻችን በሉላዊነት፣በብዙኃን መገናኛ፣(ይቅርታ ሉላዊነት ያልኩት ግሎባላይዜሽንን ነው)፣በብዙኃን መገናኛ፣በማኅበረሰብእና ይልቁንም በነሚስ ምክንያት ከሚመጣባቸው አሉታዊ ተፅዕኖ ልንከላከላቸውና ለአገራቸው ትውፊትና ለማንነታቸው ባይተዋር እንዳይኾኑ ልናንጻቸው ይገባል፡፡

ወደድንም ጠላንም ኢትዮጵያ ነገ ትልቅ አገር ትኾናለች፤ዓለምም ያያታል፡፡ ለዓለም ስንታይ ግን በራሳችን ትውፊትና ማንነታችንን መንገር በሚችል ስብእና እንጂ ፈረንጆቹ ራሳቸው የሠሩትን ቅራቅምቦ አበጃጅተን፤ከፊሉንም አበላሽተንባቸው መልሰን ብናሳያቸው ካለመታየትም ይከፋል፡፡ ሰማንያ ቋንቋ የሚነገርባት አገር ሆቴሎቿን ኔክሰስ፣ቬክሰስ፣ቦስተን፣ቻርልተን ወዘተ እያለች አትሰይምም፡፡ ሦስት ሺህ ዘመን የኖረ መሬት ዕድሜውን መግለጥና ያሳለፈውን ክፉ ደግ መተረክ የሚችልን ቅርስ ጥሎ ሌሎች የጣፉትን አይደርትም፤በሌሎች ለማማር አይጥርም፡፡ እንግዳን ማክበር እንጂ ለእንግዳ መሽሸጥ አባቶቻችን አላስተማሩንም፤ክብር ይግባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ፊደል አንድም መግባቢያችን አንድም ማንነታችን ነው፡፡ የፈረንጅ ልሳን ግን መግባቢያችን ብቻ፡፡ በመሠረቱ ታሪክ ዳቦ አይኾንም የሚል ተከራካሪ ሊኖር ይችላል፤በርግጥም አዲስ ታሪክ መሥራት ከኹሉ ይበልጣል፡፡ ኾኖም ግን ታሪክ ለመሥራት ታሪክን መሰረዝ ቅድመ ኹኔታ አይደለም፡፡ ታሪክን ጠብቆ አዲስ ታሪክ መጨመር ባለኹለት ዲናር ያደርጋል፡፡ ከሌላ የሚኮርጅ ኹል ጊዜ የተናቀ ነው፤የራሱን ዘይቤ የሚከተልና ለሕይወት የራሱ የኾነ ፍች ያለው ሕዝብ ግን ይታፈራል፤ይከበራል፡፡ በተለይ ደግሞ ጥቁሮች የራሳቸው ምንም የሌላቸውና መሠልጠንን ገና ከምዕራባውያን የሚጠብቁ ተደርገው በሚታሰቡበት ዘመን ለዚህ አስተሳሰብ የሚሽሩ ማስረጃዎች ያሏት ብቸኛ! ጥንታዊት አገር ኢትዮጵያ ናት፡

የአበውን ትውፊት ጥለን ከሥርዓት የምንደኸይ ምስኪኖች ከመኾን ይሰውረን፤አሜን!

Comment on this